በጀርመን የአሌክሳንደር ሁምቦልት ተቋም ተሸላሚው ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር

0
5238
የአሌክሳንደር ሁምቦልት
Image: Ethiopian Professor received German's Biggest Award

ማንተጋፍቶት ስለሺ, አዜብ ታደሰ – በሕይወት ዘመን ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ ነው ጀርመን ውስጥ እጅግ ታዋቂ በኾነው ተቋም ተሸላሚ የኾኑት። የተለያዩ ሀገር-በቀል ቅጠላ ቅጠሎች እና እጽዋት ላይ ምርምር በማከናወን መድኃኒቶችን ቀምመው በስማቸው አስመዝግበዋል፤ በጀርመን ሀገር ልዩ ክብር በሚሰጠው የአሌክሳንደር ሁምቦልት ተቋም ተሸላሚው ፕሮፌሰር።

በጀርመን ሀገር ልዩ ክብር በሚሰጠው የአሌክሳንደር ሁምቦልት ተቋም ለሽልማት የበቁት ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ቴክኖሎጂ ክፍል በሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የጊኦርግ ፎስተር የምርምር ተሸላሚ ለመኾን አንድ አጥኚ በሕይወት ዘመኑ ስኬታማ ሥራዎችን መፈጸም ይኖርበታል። ይኽ ስኬታማ ተግባርም በተመራማሪው የሙያ ዘርፍ እና ከዚያም ባሻገር ልዩ አስተዋጽዖ ሊኖረው ይገባል። ፕሮፌሰር ጽጌ ደግሞ የመድኃኒት ምርምር እና ሥነ-ቅመማ የረቀቁበት እና የተጠበቡበት ዘርፍ ነው፤ ለሽልማትም ያበቃቸው።

ሽልማቱ ከሐምሌ ጀምሮ ተዘጋጅቶ እንደነበር የተናገሩት ፕሮፌሰር እስካሁን ሽልማታቸውን ያልተቀበሉበትን ምክንያት ሲያብራሩ፦ «የቤት ሥራ ነበረኝ። የምጨርሳቸው ሥራዎች አሉ። የኢትዮጵያን የሣይንስ አካዳሚ ወክዬ የባዮቴክኖሎጂ ስትራቴጂ ዕቅድ ሠነድን እያዘጋጀን ነበር። አሁን ወደመጠናቀቁ ደርሷ» ሲሉ አንደኛውን ምክንያት ያስረዳሉ። «ሁለተኛው ደግሞ እዚህ እያስተማርኩ፣ ተማሪዎችንም እያማከርኩ ስለነበር አመቺ ጊዜ ለመወሰን ስል ነበር የቆየሁት። በእነሱ በኩል ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ዝግጁ ነበሩ» ሲሉ አክለዋል።

«ከእነሱ ጋር ተነጋግሬ በየካቲት ወይንም መጋቢት መጀመሪያ ላይ ከሁለት አንዱ፤ ምናልባት መጋቢት ላይ ይኾናል ወደ ጀርመን እሄዳለሁ። ሽልማቱን በተመለከተ ሁሉም ነገር፤ ደብዳቤውም ደርሶኛል። ከራሴ ጊዜ እና ከሥራ ጋር ከማመቻቸት አኳያ ነው የቆየሁት። መጋቢት ላይ በእርግጠኝነት እዛ እሄዳለሁ። እዛ ደግሞ ለተወሰኑ ወራት ምርምር ላይ እቆያለሁ» ያሉት ፕሮፌሰሩ ከሽልማቱ ሌላ ለአንድ ዓመት የሚደርስ በተለያየ ጊዜ እየተመላለሱ ከጀርመን የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በጋራ ምርምራቸውን ይቀጥላሉ።

READ  ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2020 የአለማችን 66ኛዋ ባለ ትልቅ ኢኮኖሚ ሀገር ትሆናለች

ፕሮፌሰር ጽጌ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ እጽዋት እና ቅጠላቅጠሎች መድኃኒቶችን ቀምመው ሠርተዋል። ለአብነት ያኽልም መተሬ ከሚባለው ቅጠል የሠሩት መድሃኒት ከትንሿ አንጀት እንደ ኮሦ ያሉ ሕዋሳትን ያስወግዳል። ፕሮፌሰሩ ከእዚህ ቅጠል በእንክብል መልክ መድሃኒት አዘጋጅተዋል። ፕሉምባጎ ዛይሌኒካ ከሚባለው እጽ ደግሞ ችፌን ለማከም የሚውል መድሃኒት ቀምመዋል። ችፌ ቆዳ ላይ ሽፍ ብሎ የሚያሳክክ ስር የሰደደ ቁስል ነው። መድሃኒቶቹ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ በማድረግ ዓለም አቀፍ ዕውቅናም በስማቸው አስመዝግበዋል። ፕሮፌሰር ጽጌ በስማቸው ያስመዘገቧቸው መድሃኒቶች እነዚህ ሁለቱ ብቻ አይደሉም።

በርካታ መድኃኒቶችንም ሀገር በቀል የሆኑ እጽዋትን በመቀመም ሠርተዋል። «ሌሎችም አሉ፤ እዚህ ሀገር ብቻ የሚገኙ እጽዋቶች አሉ። ለምሳሌ በተለምዶ የኪንታሮት በሽታ ለምንለው ቅባት ሠርተናል። ያ ቅባት ኪንታሮትን ያስታግሳል። በኪኒን ደረጃ ከማርቲን ሉተር ዩኒቨርሲቲ ጋር፣ ከእነ ፕሮፌሰር ኖይበርት ጋር በመተባበር፣ በክኒን ደረጃ ሠርተን፣ በቤተ-ሙከራ ደረጃ የሚቆጣ የሰውነት አካልን ሊያስታግስ የሚችል ንጥረ-ነገር ከውስጣቸው አውጥተን ሠርተናል።»

ፕሮፌሰር ጽጌ የሠሩት ይኼ ብቻ አይደለም። «እንደገና ደግሞ መድኃኒት የሌላቸው፤ በተሐዋሲ ሊመጡ የሚችሉ፣ በሽታዎችን ሊያክሙ የሚችሉ ከኢትዮጵያ እጽዋት የወጡ ንጥረ-ነገሮችን አውጥተን ፈዋሽነታቸውን በቤተ-ሙከራ ደረጃ አረጋግጠናል፤ በእርግጥ ሰው ላይ አልተሞከረም። በርካታ እጽዋቶች አሉ ከእዚህ አንፃር የፈተሽናቸው» ብለዋል።

ፕሮፌሰር ጽጌ መድኃኒቶቹን የሚሠሩት ብዙውን ጊዜ ከባሕላዊ ሐኪሞች ጋር በመመካከር ነው። እንደ ጀርመን ባሉ የበለጸጉ ሃገራትም ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ሀገር በቀል ዕውቀትን መሠረት ያደረጉት ባሕላዊ ህክምናዎች ላይ ማተኮር ጠቃሚ እንደሆነም ገልጠዋል። ሆኖም የምርምር ውጤቶች ኅብረተሰቡ ጋር ለመድረስ በርካታ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

READ  ሳቂታዋ ቢሸፍቱ በእንባ ፈጣሪን ያመሰገነችበት ቀን

«የታዳጊ ሃገራት የምርምር ውጤቶች ኅብረተሰቡ ጋር ለመድረስ የዩኒቨርሲቲ፣ የምርምር ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ትስስር ያስፈልጋል። ይኼ ትስስር ጠንካራ አይደለም። እንደውም ውጪ ያሉት የመንግሥት፣ የኢንዱስትሪ፣ የምርምር ወይንም ዩኒቨርሲቲዎች ስር ያሉ የምርምር ተቋማት ትስስር ይጠይቃል።

ከዚህ አልፎ በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡም የሚካፈልበት ነው» ይላሉ። ፕሮፌሰር ጽጌ የአንድ የምርምር ውጤት ወደ ኅብረተሰቡ እንዲደርስ ወሳኝ ነጥቦችን ያብራራሉ። «የባሕል መድኃኒት አዋቂዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ ኢንዱስትሪ እና የመንግሥት ትብብር የግድ ያስፈልጋል» ሲሉ አራቱን ወሳኝ ተቋማት ጠቅሰዋል።

የእነዚህ ተቋማት ትስስር በታዳጊ ሃገራት ውስጥ ጠንካራ አለመኾኑን ግን ያሰምሩበታል። «ትስስሩ እንዲፈጠር፣ ምርምሩ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲደርስ ወደ መጨረሻ ተገልጋዩ ኅብረተሰብ ክፍል እንዲደርስ ይኽ ትስስር ያስፈልጋል» ሲሉ ተናግረዋል። More Here

NO COMMENTS