የኢትዮጵያ መንግስት ለ140 የኤርትራ ስደተኛ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ሰጠ

0
3066
የኤርትራ ስደተኛ
Image: Eritrean Refugee

ሽሬ እንዳስላሴ ጥቅምት 17/2009 የኢትዮጵያ መንግስት 140 የኤርትራ ስደተኛ ተማሪዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው እንዲማሩ የትምህርት ዕድል መስጠቱን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች አስተዳደር አስታወቀ።

በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ከትናንት በስቲያ ሽኝት የተደረገላቸው ስደተኛ ተማሪዎቹ ለመማር ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ምስጋና ሊቸረው እንደሚገባ ገልጸዋል።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች አስተዳደር የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አስተባባሪ አቶ ተኪኤ ገብረየሱስ በሽኝት ስነ-ስርአቱ ላይ እንደተናገሩት፣ የትምህርት ዕድሉ ከተሰጣቸው አጠቃላይ ስደተኛ ተማሪዎች መካከል 80ዎቹ በዞኑ በሚገኙ አራት የስደተኞች መጠሊያ ጣቢያዎች የነበሩ ናቸው።

ቀሪዎቹ 60 ስደተኛ ተማሪዎች ከአዲስ አበባ ከተማ የመጡ ሲሆኑ፣ የትምህርት ዕድል ከተሰጣቸው ተማሪዎች ውስጥ ሰባቱ ሴት መሆናቸውን አስተባባሪው አስረድተዋል።

አቶ ተኪኤ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት ለስደተኞች ከትምህርት ዕድል በተጨማሪ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እንደማንኛውም ዜጋ ሰርተው እንዲኖሩና ሌሎች መሰል እድሎችን በማመቻቸት ላይ ነው።

በቀጣይም መንግስት ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ነው አቶ ተኪኤ የገለጹት።

የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑ ስደተኛ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ዮናስ አሸብር በኤርትራ እያለ የትምህርት ጥማት የነበረው ቢሆንም እስካሁን ድረስ የመማር ዕድል ሳያገኝ መቆየቱን ተናግሯል።

“የብዙ ዓመታት የመማር ምኞቴን ያሳካልኝን የኢትዮጵያ መንግስትን አመሰግናለሁ” ያለው ተማሪ ዮናስ፣ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኤርትራውያን ለኢትዮጵያ መንግስት ምስጋና ሊያቀርቡ እንደሚገባ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራውያን ስደተኞችን ለማገዝ እያደረገው ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ የሁለቱ ሀገራት የቀጣይ ግንኙነት መሰረት ሊሆን እንደሚችል ያለውን እምነት ገልጿል።

READ  Zlin-143-102 የሚባል የኤርትራ አየር ኃይል መለማመጃ አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ ኮበለለ

የትምህርት ዕድል በማግኘቱ መደሰቱን የገለጸው ሌላው ስደተኛ ተማሪ ሳዕረ ሳህለ፣ “የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገው ያለውን በጎ ተግባር በማስተዋወቅ በኩል ኤርትራውያን ስደተኞች አምባሳደር መሆን አለብን” ብሏል።

የዓለም ማህበረሰብም የኢትዮጵያን መንግስት ተግባር በአዎንታዊነት ተቀብሎ ምስጋና ሊቸር እንደሚገባ አመልክቷል።

ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመግባት በቅድሚያ የመግቢያ ፈተና መውሰዳቸውን የገለጸው ወጣት ሳዕረ፣ በትምህርት ቆይታው በርትቶ በመማር ውጤታማ ለመሆን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቋል።

የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ተወካይ ሚስ ሶፊ ሎጎ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ ስደተኞችን ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው እንዲማሩ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞቹን ከመቀበል ባለፈ ከዜጎቹ ጋር መማር እንዲችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ተወካዩ አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ለአንድ ሺህ 500 ኤርትራውያን ስደተኞች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብተው እንዲማሩ ማድረጉን አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡ ENA

NO COMMENTS