ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2020 የአለማችን 66ኛዋ ባለ ትልቅ ኢኮኖሚ ሀገር ትሆናለች

0
2811
ትልቅ ኢኮኖሚ
Image: Ethiopian Economy

(ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 የአለማችን 66ኛዋ ባለ ትልቅ ኢኮኖሚ ሀገር እንደምትሆን ተገለፀ።

ፋይናንሽያል ታይምስ ጋዜጣ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ እንደዘገበው ሀገሪቱ በ2005 የነበረችበትን 103ኛ ደረጃ በ37 ደረጃ አሻሽላ ነው በ2020 የአለማችን 66ኛዋ ባለ ትልቅ ኢኮኖሚ ሀገር የምትሆነው።

ኢትዮጵያ እንደነ ኬንያ፣ ጓቲማላ እና ቡልጋሪያ የመሰሉ ሀገራትን በመቅደም ነው ደረጃውን የምትይዘው ብሏል ዘገባው።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት 12 አመታት በአማካይ የ10 በመቶ እድገት አስመዝግቧል ያለው ፋይናንሽያል ታይምስ፥ ይሄው እድገት በቀጣዮቹ አመታትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክቷል።

የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት አሁንም በግብርና ምርቶች በከፍተኛ ደረጃ ይደገፋል፤ በመንግስት ስር ያሉ ዘርፎች እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም ኢኮኖሚዊ እድገቱን ያቀላጥፋሉ ነው ያለው ዘገባው።

FDF
Image: IMF

አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤትነትን በቅርቡ ከኬንያ እንደምትረከብ መግለጹ ይታወሳል።

አይ ኤም ኤፍ የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተመለከተበት ሪፖርቱ፥ ኢትዮጵያ በተያዘው የፈረንጆቹ አመት የቀጠናውን የኢኮኖሚ መሪነት ከኬንያ እንደምትረከብ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ ለተከታታይ 10 አመታት ባለ ሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገቧን የጠቀሰው ሪፖርቱ፥ እየተመዘገበ ያለው እድገት የህዝብ መገልገያ መሰረት ልማቶችን ያማከለ መሆኑንም ገልጿል።

ጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት እድገቱም ባለፈው አመት ከነበረበት 61 ነጥብ 62 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በዚህ አመት ወደ 69 ነጥብ 21 ቢሊየን ዶላር እንደሚያድግም ነው የተቋሙ ሪፖርት የጠቀሰው።

ይህም ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት በቀሩት የፈረንጆቹ አመት ከነበረበት 63 ነጥብ 39 ቢሊየን ዶላር ወደ 69 ነጥብ 17 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያድግ ከሚጠበቀው የኬንያ ጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት እድገት አንጻር ከፍ ያለ መሆኑም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

READ  Ethiopia Set to Produce Gold by Next Year

የኬንያ ጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት እድገት በፈረንጆቹ 2000 ላይ ከኢትዮጵያ ከ71 በመቶ በላይ ብልጫ እንደነበረው ያወሳው ሪፖርቱ፥ ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ባስመዘገብችው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ልዩነቱ መጥበቡንም ነው የገለጸው።

ይህ የኢኮኖሚ መሪነት ሃገሪቱን የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ የተያዘውን እድገት ለማስቀጠል እንደሚረዳም ነው የተቋሙ ሪፖርት የሚያመለክተው።

ተቋሙ በሪፖርቱ እንደገለጸው፥ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ የዜጎችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ መሰረተ ልማቶች የተደገፈ እና ቀጣይነት ያለው ነው።

ከዚህ ባለፈም ሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ለማስቀጠል የሚረዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ መሆኗም በሪፖርቱ ጠቅሷል።

NO COMMENTS