የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካርቱም ቅርንጫፉን ሊከፍት ነው

0
2340
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Image: CBE - News.et

አዲስ አበባ ጥቅምት 11/2009 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ቅርንጫፉን እንደሚከፍት ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው የኢትዮ-ሱዳን የኢኮኖሚ የቴክኒክ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ያካሄደው አራተኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ በተጠናቀቀበት ወቅት ነው።

አገራቱ በእንስሳት ኃብት፣በትራንስፖርት፣በባቡር መስመር ፣በባንክ አገልግሎትና በመሳሰሉ መስኮች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነቶችም ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ተገልጿል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እንዳሉት አገራቱ ምጣኔ ኃብታዊ ግንኙነታቸውን የሚያሳልጡ መሰረተ ልማቶች በጋራ ለማልማት እየሰሩ ነው።

የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ካርቱም እንዲከፈት ስምምነት ላይ መደረሱ የዚሁ ትብብር አንዱ አካል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የባንኩን ቅርጫፍ በካርቱም ለመክፈት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል ያሉት ሚኒስትሩ የህም በሁለቱ አገራት መካከል ቀልጣፋና ምቹ የክፍያ ስርዓት በመዘርጋት የንግድ እንቅስቃሴውን ያሳልጠዋል ብለዋል።

በመኪና እና የባቡር መሰረተ ልማት ለመተሳሰር የሚያስችል ስምምነት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ የኢትዮ-ሱዳን የኢኮኖሚ የቴክኒክ ኮሚቴ የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በማጠናከር በኩል ውጤታማ እየሆነ መጥቷል።

ለሚመሰረተው የኢትዮ-ሱዳን የኢንዱስትሪ ፓርክ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት መከፈቱና ሁለቱን አገራት በባቡር መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የተደረገው ስምምነት ኮሚቴው ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በስኬት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

የሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንትና የኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ሀሳቦ መሀመድ በበኩላቸው የአገራቱ ህዝቦች ካሏቸው ኃብት ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል ብለዋል።

ሁለቱ አገራት በጋራ የሚያለሟቸው መሰረተ ልማቶች መኖራቸውና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርጫፍ በካርቱም መከፈት የአገራቱን የንግድ እንቅስቃሴ በማፋጠን የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋግጣልም ነው ያሉት።

READ  መፍትሔ የምናመጣው ‹‹ስለተናገርን›› ሳይሆን ‹‹ከተደመጥን ብቻ›› ነው፡፡

አገራቱ በተለይ በርካታ የእንስሳት ኃብት ስላላቸው ዘርፉን ከሕገ-ወጥ ድርጊቶች በመከላከል ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ይኖርባቸዋል ብለዋል። ENA

NO COMMENTS