ፌስቡክ ይዘጋ! አዲሱ የማናለብኝ ባዮች ነጠላ ዜማ

0
5278
ፌስቡክ ይዘጋ
Image: ፌስቡክ ይዘጋ

ፌስቡክ ይዘጋ! አዲሱ የማናለብኝ ባዮች ነጠላ ዜማ፤ ኢህአዴግን ከስራ አስፈጻሚው ይልቅ ደጋፊ ነን ባይ ፌስቡከሮቹ የሚመሩት ይመስለኛል፡

ከስናፍቅሽ አዲስ ሰሞኑን የኢህአዴግ ደጋፊ ነን የሚሉ የፌስቡክ ቡድኖች “ኢትዮጵያም እንደ ቻይና ፌስቡክ ትዝጋ” የሚል ዘመቻ ላይ ናቸው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ “ህዝቡ የደረሰበት ንቃተ ህሊና ፌስቡክን ለመጠቀም አልደረሰም፤ ሀገር በፌስቡክ እየታመሰ ነው!!” የሚል ነው፡፡ ሁኔታው እያሳዘነኝ ነው፡፡ የሆነ ትምህርትም ህይወትም አልሆን ያለው ወጣት ራሱን ለማስመለጥ ሊግ ምናምን ይቀላቀልና ከዚያ ይሄ ህዝብ ለፌስቡክ አልበቃም ይዘጋ ብሎ ሀገር ይኮንናል፡፡

ኢህአዴግ እነዚህን ደጋፊዎቹን በሆነ ጆሮው እንደሚያደምጣቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ አንዳንዴ ከዛቻቸው እና ከፉከራቸው ማግስት የሚሆነውን ሳስብ ከግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ይልቅ በእነዚህ ጥቂት እንደግፍሃለን ባይ ፌስቡከሮች የሚመራ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ የኢህአዴግ ናቸው ወይስ የሌላ እስከአሁንም አከራካሪ ሆኗል፡፡

ለምን መሰላችሁ? ለምሳሌ ገዱ አንዳርጋቸው ተነሱ ያሉት እነሱ ናቸው፡፡ ሽፈራሁ ሽጉጤ ተወገዱ ብለውም ጽፈው ነበር፡፡ አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ አለምነውን፣ አቶ ገዱን ፎቶ ለጥፈው ትምህክተኛው ብአዴን ሲሉ በአደባባይም ዘልፈዋል፡፡ ስለዚህ እነማን ናቸው በሚለው ላይ ክርክር አለ፡፡ መከልከል መፍትሔ የሆነባትን ኢትዮጵያ ልጠላት ነው፡፡

Watch The Social Media Boom in Ethiopia

መስቀል አደባባይ ሰልፍ ተካሂዶ ከተበጠበጠ ከዛሬ ጀምሮ መስቀል አደባባይ ሰልፍ ተከልክሏል፡፡ ቪኤኤ መረጃ አዛብቶብናል ከተባለ ጃም ይደረግ፤ አሁን ደግሞ ፌስቡክ ለሀገሪቱ ብጥብጥ አደጋ ሆኗል እና ይዘጋ፡፡ መዝጋት፣ ማገድ፣ መከልከል መፍትሔ ነው ብለው የሚያምኑ ተተኪ አባላት ያሉት ፓርቲ በመሆኑ በእርግጥም ኢህአዴግ አሳዝኖኛል፡፡ ነገ ጃዋር ጥሬ ስጋ ከወደደ እኛ ልንከለከል ነው፡፡ ዶክተር ብርሃኑ የአስቴርን ሙዚቃ ከወደደ ካሴቷን ልንለቅም ነው፡፡

READ  ጎንደር በቤተክርስቲያን አባቶችና በህዝቡ ውሳኔ የደመራን በዓል ሳታከብር ውላለች

ልክ የዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳን መጽሐፍ እንደለቀምንው፡፡ ይሄ ለሀገር መፍትሔ አይደለም፡፡ ፌስቡክ ቀስቅሶአቸው አይመስለኝም የዛሬ አርባ አመት ጥቂቶች ቆራጦች በርሃ የገቡት፡፡ እናም ፌስቡክን ከእኩይ አላማው ጋር ብቻ አቆራኝቶ ዝጋው ብሎ መንግስት ላይ መጮህ የሰሞኑ ትንንሽ መንግስታት አጀንዳ መሆኑን አልወደድኩትም፡፡ ፌስቡክ ለእኛ ከእናንተ አስተሳሰብ ባሻገር ትርጉም ያለው ነገር ነው፡፡

እናንተ ሁለታችሁም ወገኖች ፌስቡክን ከምትጠቀሙበት አግባብ ወጣ ብሎ የሚጠቀመውን ሰው መናቅም ደግ አይመስለኝም፡፡ ለእኔ ሁለታችሁም ያው ስለሆናችሁ ነው፡፡ ለእናንተ ፌስቡክ የጃዋርን ፎቶ ተቃዋሚው ሲለቅ የዶክተር ደብረ ጺዮንን በመልቀቅ ማጥለቅለቅ፤ መለስ ዜናዊ ያ ሲለጥፍ ያ በእልፍ ዶክተር ብርሃኑ ነጋን ገጭ ማድረግ፤ ከዚያ በእናንተ ልክ ሀገር ተመዝና ኢትዮጵያውያንን ፌስቡክ እያጠፋቸው ነው ስለዚህ ይዘጋ ብሎ መጮህ፤ አንዳችሁ ከአንዳችሁ ስለማትሻሉ እናንተን በመውቀስ ጊዜ ማባከኑ ከንቱ ነው፡፡

ኢህአዴግ ነን ባዮች ታላቁ የሰው ልጅ ሞቶ አሟሟት ስትተነትኑ ቁጥር ስትሸራርፍ ይሄንን ካላመንክ ብላችሁ ስትጮሁ ትውላላችሁ፡፡ መንግስትን እጥላለሁ ባዩ ደግሞ የሞተው ወንድማችን አሟሟት ልብ ሰባሪነት መጠኑ አንሶብህ ሶሪያ ፍርስራሽ ስር የተጋደመውን ሬሳ ኢትዮጵያ እያልክ፣ በሜካፕ የተቦደሰውን ፊት በከባድ መሳሪያ ሰው ጨረሱ ስትል እመኑ ትላለህ፡፡ አይቻልም እንጂ ሁለታችሁም የሌላችሁበት ኢትዮጵያ ብትኖረን እንዴት በሰላም በኖርን፡፡ እናም ኢትዮጵያ የታላቅ ህዝብ ሀገር ናት፡፡ ታላቅ ምድር ናት፡፡ በእናንተው ልክ እኛን አትስፈሩን፡፡

የሰሞኑ ነጠላ ዜማም ያሳሰብ እንዲህ ፌስቡክ ሰው አጫረሰ ይዘጋልን ከሚለው ጫጫታችሁ ስጋት ቢጤ ስለገባኝ ነው፡፡ እኔ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ በላይ የእናንተ ፉከራ ሲሆን ስላየሁት እባካችሁ ተውን ማለትም የምፈልገው እናንተን ነው፡፡ መንግስትም እናንተ ናችሁ፡፡

READ  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትጥቅ የማስፈታት አላማ እንደሌለው ተገለፀ

PM Hailemariam Desalgn Talks about the Social Media

NO COMMENTS